ምዕራፍ 13
1፤ ኤፍሬም በተናገረ ጊዜ ፍርሃት ነበረ፥ በእስራኤልም ዘንድ ታበየ፤ ነገር ግን በኣልን በማምለክ በበደለ ጊዜ ሞተ።
2፤ አሁንም ኃጢአትን ይሠሩ ዘንድ ጨመሩ፤ በብራቸውም ለራሳቸው ቀልጦ የተሠራ ምስልን፥ እንደ ጥበባቸውም ጣዖታትን ሠርተዋል፤ ሁሉም የሠራተኛ ሥራ ናቸው። ስለ እነርሱም። የሚሠዉ ሰዎች እምቦሳውን ይሳሙ ይላሉ።
3፤ ስለዚህም እንደ ማለዳ ደመና፥ በጥዋትም እንደሚያልፍ ጠል፥ በዐውሎ ነፍስም ከአውድማ እንደሚበተን እብቅ፥ ከመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ።
4፤ እኔ ግን ከግብጽ ምድር ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፥ ከእኔም በቀር ሌላ መድኃኒት የለም።
5፤ በምድረ በዳ፥ እጅግ በደረቀ ምድር አውቄህ ነበር።
6፤ ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ፥ በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ፤ ስለዚህ ረሱኝ።
7፤ ስለዚህም እኔ እንደ አንበሳ ሆንሁባቸው፥ እንደ ነብርም በመንገድ አጠገብ አደባባቸዋለሁ፤
8፤ ልጅዋ እንደ ተነጠቀባት ድብ እገጥማቸዋለሁ፥ የልባቸውንም ስብ እቀድዳለሁ፤ በዚያም እንደ አንበሳ እበላቸዋለሁ፥ የምድረ በዳም አውሬ ይነጣጠቃቸዋል።
9፤ እስራኤል ሆይ፥ በእኔ በረዳትህ ላይ በመነሣትህ ጥፋትህ ነው።
10፤ በየከተማህ ሁሉ ያድንህ ዘንድ ንጉሥህ ወዴት አለ? ስለ እነርሱም። ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ ብለህ የተናገርኸው መሳፍንቶችህ ወዴት አሉ?
11፤ በቍጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፥ በመዓቴም ሻርሁት።
12፤ የኤፍሬም በደል ታስሮአል፥ ኃጢአቱም ተከማችቶአል።
13፤ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤ በሚወለድበት ጊዜ በማኅፀን አፍ ቀጥ ብሎ አይወጣምና አእምሮ የሌለው ልጅ ነው።
14፤ ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፥ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፥ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ማጥፋትህ ወዴት አለ? ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች።
15፤ በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆን የምሥራቅ ነፋስ ይመጣል፥ የእግዚአብሔር ነፋስ ከምድረ በዳ ይመጣል፤ ምንጩንም ያደርቃል፥ ፈሳሹንም ያጠፋል፥ የተከበሩ ዕቃዎች ሁሉ ያሉበትን መዝገብ ይበዘብዛል።
16፤ ሰማርያ በአምላክዋ ላይ ዐምፃለችና በደልዋን ትሸከማለች፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ሕፃኖቻቸውም ይፈጠፈጣሉ፥ እርጕዞቻቸውም ይቀደዳሉ።