ትንቢተ ዳንኤል - Daniel

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 3

1፤ ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው።
2፤ ንጉሡም ናቡከደነፆር መኳንንትንና ሹማምቶችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፥ መጋቢዎችንም፥ አውራጃ ገዦችንም ሁሉ ይሰበስቡ ዘንድ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ።
3፤ በዚያን ጊዜም መኳንንቱና ሹማምቶቹ፥ አዛዦቹና አዛውንቶቹ፥ በጅሮንዶቹና አማካሪዎቹ፥ መጋቢዎቹና አውራጃ ገዦቹ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ተሰበሰቡ፤ ናቡከደነፆርም ባቆመው ምስል ፊት ቆሙ።
4፤ አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ፥
5፤ የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል።
6፤ ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።
7፤ ስለዚህ በዚያን ጊዜ አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የተናገሩ ሁሉ ተደፉ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ሰገዱ።
8፤ በዚያን ጊዜም ከለዳውያን ቀርበው አይሁድን ከሰሱ።
9፤ ለንጉሡም ለናቡከደነፆር ተናገሩ እንዲህም አሉ። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ።
10፤ አንተ፥ ንጉሥ ሆይ። የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ የሚሰማ ሰው ሁሉ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ይስገድ፤
11፤ ተደፍቶም የማይሰግድ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል ብለህ አዘዝህ።
12፤ በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ የሾምሃቸው ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም የሚባሉ አይሁድ አሉ፤ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ትእዛዝህን እንቢ ብለዋል፤ አማልክትህን አያመልኩም፥ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል አይሰግዱም።
13፤ ናቡከደነፆርም በብስጭትና በቍጣ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፤ እነዚህንም ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው።
14፤ ናቡከደነፆርም። ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን?
15፤ አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን የመሰንቆውንና የክራሩን የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው።
16፤ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም። ናቡከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም።
17፤ የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ!
18፤ ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።
19፤ የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፥ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፤ እርሱም ተናገረ፥ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት አዘዘ።
20፤ ሲድራቅንና ሚሳቅንም አብደናጎንም ያስሩ ዘንድ፥ ወደሚነድድም ወደ እቶን እሳት ይጥሉአቸው ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ከነበሩት ኃያላን አዘዘ።
21፤ የዚያን ጊዜም እነዚህ ሰዎች ከሰናፊላቸውና ከቀሚሳቸው ከመጐናጸፊያቸውም ከቀረውም ልብሳቸው ጋር ታስረው በሚነድድ በእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ።
22፤ የንጉሡም ትእዛዝ አስቸኳይ ስለሆነ የእቶኑም እሳት እጅግ ስለሚነድድ፥ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው።
23፤ እነዚህም ሦስቱ ሰዎች ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ታስረው በሚነድደው በእቶኑ እሳት ውስጥ ወደቁ።
24፤ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም። ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም። ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት።
25፤ እርሱም። እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ።
26፤ የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ። እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅም አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ።
27፤ መሳፍንቱና ሹማምቶቹም አዛዦቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃይል እንዳልነበረው፥ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተቃጠለች፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ።
28፤ ናቡከደነፆርም መልሶ። መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ።
29፤ እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቈረጣሉ፥ ቤቶቻቸውም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ።
30፤ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው።