መጽሐፈ ነህምያ። - Nehemiah

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13


ምዕራፍ 13

1፤ በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ በሕዝቡ ጆሮ አነበቡ፤ አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ።
2፤ የእስራኤልን ልጆች በእንጀራና በውኃ ስላልተቀበሉአቸውና ይረግማቸው ዘንድ በለዓምን ስለ ገዙባቸው ነው፤ ነገር ግን አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት መለሰው።
3፤ ሕጉንም በሰሙ ጊዜ ድብልቁን ሕዝብ ሁሉ ከእስራኤል ለዩ።
4፤ ከዚህም አስቀድሞ በአምላካችን ቤት ጓዳዎች ላይ ተሾሞ የነበረው ካህኑ ኤልያሴብ ከጦቢያ ጋር ተወዳጅቶ፥
5፤ ለሌዋውያን፥ ለመዘምራን፥ ለበረኞቹ እንደ ሕጉ የተሰጣቸውን የእህሉን ቍርባንና ዕጣኑን፥ ዕቃዎቹንም፥ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት፥ ለካህናቱም የሆነውን የማንሣት ቍርባን አስቀድሞ ያስቀመጡበትን ታላቁን ጓዳ አዘጋጅቶለት ነበር።
6፤ እኔ ግን በባቢሎን ንጉሥ በአርጤክስስ በሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበርና በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም። ከጥቂት ዘመንም በኋላ የንጉሡን ፈቃድ ለመንሁ፤
7፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣሁ፤ ኤልያሴብም በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦብያ ጓዳውን በማዘጋጀት ያደረገውን ክፉ ነገር አስተዋልሁ።
8፤ እጅግም አስከፋኝ፤ የጦብያንም የቤቱን ዕቃ ሁሉ ከጓዳ ወደ ውጪ ጣልሁ።
9፤ ጓዳዎቹንም እንዲያነጹ አዘዝሁ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃዎች የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም መልሼ በዚያ አገባሁ።
10፤ ለሌዋውያንም እድል ፈንታቸው እንዳልተሰጠ፥ የሚያገለግሉትም ሌዋውያንና መዘምራን እያንዳንዱ ወደ እርሻው እንደ ሄዱ ተመለከትሁ።
11፤ እኔም። የእግዚአብሔር ቤት ስለ ምን ተተወ? ብዬ ከአለቆቹ ጋር ተከራከርሁ። ሰበሰብኋቸውም፥ በየስፍራቸውም አቆምኋቸው።
12፤ ይሁዳም ሁሉ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት ወደ ዕቃ ቤቶች አመጡ።
13፤ በዕቃ ቤቶችም ላይ ካህኑን ሰሌምያን፥ ጸሐፊውንም ሳዶቅን፥ ከሌዋውያኑም ፈዳያን ሾምሁ፤ ከእነርሱም ጋር የመታንያ ልጅ የዘኩር ልጅ ሐናን ነበረ፤ እነርሱም የታመኑ ሆነው ተገኙ፥ ሥራቸውም ለወንድሞቻቸው ማከፋፈል ነበረ።
14፤ አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ አስበኝ፤ ለአምላኬም ቤት ያደረግሁትን ወረታዬን አታጥፋ።
15፤ በዚያም ወራት በይሁዳ በሰንበት ቀን የወይን መጥመቂያን የሚረግጡትን፥ ነዶም የሚከመሩትን፥ የወይኑን ጠጅና የወይኑን ዘለላ በለሱንም ልዩ ልዩም ዓይነት ሸክም በአህዮች ላይ የሚጭኑትን፥ በሰንበትም ቀን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያስገቡትን አየሁ፤ ገበያ ባደረጉበትም ቀን አስመሰከርሁባቸው።
16፤ ደግሞም በእርስዋ የተቀመጡ የጢሮስ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ዓሣዎችን ልዩ ልዩም ዓይነት ሸቀጥ አምጥተው በሰንበት ቀን በኢየሩሳሌም ለይሁዳ ልጆች ይሸጡ ነበር።
17፤ ከይሁዳም ታላላቆች ጋር ተከራከርሁና። ይህ የምታደርጉት ክፉ ነገር ምንድር ነው? የሰንበትንስ ቀን ታረክሳላችሁን?
18፤ አባቶቻችሁ እንደዚህ አድርገው አልነበረምን? አምላካችንስ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ በእኛና በዚህ ከተማ ላይ አምጥቶ አልነበረምን? እናንተም ሰንበትን በማርከሳችሁ በእስራኤል ላይ መዓትን ትጨምራላችሁ አልኋቸው።
19፤ ከዚህ በኋላ ከሰንበት በፊት በኢየሩሳሌም በሮች ድንግዝግዝታ በሆነ ጊዜ በሮችዋ እንዲዘጉ፥ ሰንበትም እስኪያልፍ ድረስ እንዳይከፈቱ አዘዝሁ። በሰንበትም ቀን ሸክም እንዳይገባ ከብላቴኖቼ በአያሌዎቹ በሮችዋን አስጠበቅሁ።
20፤ ሁሉም አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በኢየሩሳሌም ውጭ አድረው ገበያ አድርገው ነበር።
21፤ እኔም አስመሰከርሁባቸውና። በቅጥሩ ውጭ ለምን ታድራላችሁ? እንደ ገና ብታደርጉት እጆቼን አነሣባችኋለሁ አልኋቸው። ከዚያም ወዲያ በሰንበት ቀን እንደ ገና አልመጡም።
22፤ ሌዋውያኑንም ራሳቸውን እንዲያነጹ፥ መጥተውም በሮቹን እንዲጠብቁ፥ የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ ነገርኋቸው። አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ደግሞ አስበኝ፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ራራልኝ።
23፤ ደግሞም በዚያ ወራት የአዛጦንና የአሞንን የሞዓብንም ሴቶች ያገቡትን አይሁድ አየሁ።
24፤ ከልጆቻቸውም እኵሌቶቹ በአዛጦን ቋንቋ ይናገሩ ነበር፥ በአይሁድም ቋንቋ መናገር አያውቁም ነበር።
25፤ ከእነርሱም ጋር ተከራከርሁ፥ ረገምኋቸውም፤ ከእነርሱም አያሌዎቹን መታሁ፥ ጠጉራቸውንም ነጨሁ፥ እንዲህም ብዬ በእግዚአብሔር አማልኋቸው። ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለእናንተና ለልጆቻችሁ አትውሰዱ።
26፤ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በዚህ ነገር ኃጢአት አድርጎ የለምን? በብዙ አሕዛብም መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፥ በአምላኩም ዘንድ የተወደደ ነበረ፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ አንግሦት ነበር፤ እርሱንም እንኳ እንግዶች ሴቶች አሳቱት።
27፤ በውኑ ይህን ሁሉ ታላቅ ክፋት እንሠራ፥ እንግዶችንም ሴቶች በማግባት አምላካችን እንበድል ዘንድ እናንተን እንስማ?
28፤ ከዋነኛውም ካህን ከኤልያሴብ ልጅ ከዮአዳ ልጆች አንዱ ለሖሮናዊው ለሰንባላጥ አማች ነበረ፤ ከእኔም ዘንድ አባረርሁት።
29፤ አምላኬ ሆይ፥ ክህነትን የክህነትንና የሌዋውያንንም ቃል ኪዳን ስላፈረሱ አስባቸው።
30፤ ከእንግዳ ነገርም ሁሉ አነጻኋቸው፤ ለካህናቱና ለሌዋውያኑም እያንዳንዳቸው በየሰሞናቸው፥
31፤ በየጊዜያቸውም ለእንጨት ቍርባን ለበኵራቱም ሥርዓት አደረግሁ። አምላኬ ሆይ፥ በመልካም አስበኝ።