መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ። - 1 Chronicles

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 19

1፤ ከዚህም በኋላ የአሞን ልጆች ንጉሥ ናዖስ ሞተ፥ ልጁም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
2፤ ዳዊትም። አባቱ ስላደረገልኝ ወረታ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ልያጽናናው መልእክተኞችን ላከ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ሊያጽናኑት ወደ ሐኖን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ።
3፤ የአሞን ልጆች አለቆች ግን ሐኖንን። ዳዊት አባትህን አክብሮ የሚያጽናኑህን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ባሪያዎቹስ አገሪቱን ለመመርመር፥ ለማጥፋት፥ ለመሰለልም ወደ አንተ የመጡ አይደሉምን? አሉት።
4፤ ሐኖንም የዳዊትን ባሪያዎች ወስዶ አስላጫቸው፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው።
5፤ ወሬኞችም ሄደው በሰዎቹ ላይ የተደረገውን ለዳዊት አስታወቁት። ሰዎቹም በብዙ አፍረዋልና ተቀባዮች ላከ፤ ንጉሡም። ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ አለ።
6፤ የአሞንም ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባዩ ጊዜ ሐኖንና የአሞን ልጆች ከመስጴጦምያ፥ ከአራምመዓካ፥ ከሱባ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ይቀጥሩ ዘንድ አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ።
7፤ ሠላሳ ሁለትም ሺህ ሰረገሎች የመዓካንም ንጉሥ ሕዝቡንም ቀጠሩ፤ መጥተውም በሜድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአሞንም ልጆች ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ወደ ሰልፍ መጡ።
8፤ ዳዊትም ይህ በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ።
9፤ የአሞንም ልጆች ወጥተው በከተማይቱ በር አጠገብ ተሰለፉ፤ የመጡትም ነገሥታት ለብቻቸው በሜዳው ላይ በሩ።
10፤ ኢዮአብም በፊትና በኋላ ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦችን ሁሉ ለይቶ በሶርያውያን ላይ አሰለፋቸው።
11፤ የቀረውንም ሕዝብ ለወንድሙ ለአቢሳ ሰጠው፥ በአሞንም ልጆች ላይ ተሰለፉ።
12፤ እርሱም። ሶርያውያን ቢበረቱብኝ እርዳኝ፤ የአሞንም ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ።
13፤ አይዞህ፥ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።
14፤ ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ለሰልፍ ወደ ሶርያውያን ፊት ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ።
15፤ የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ። ኢዮአብም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
16፤ ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ መልእክተኞች ልከው በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን አስመጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሾፋክ በፊታቸው ነበረ።
17፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ መጣባቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊትም በሶርያውያን ላይ በተሰለፈ ጊዜ እነርሱ ከእርሱ ጋር ተዋጉ።
18፤ ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞች፥ አርባ ሺህም እግረኞች ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሾፋክን ገደለ።
19፤ የአድርአዛርም ባሪያዎች በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ታረቁ፥ ገበሩለትም፤ ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ እንቢ አሉ።