መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ - 1 Samuel

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31


ምዕራፍ 13

1፤ ሳኦልም በእስራኤል ላይ ሁለት ዓመት ከነገሠ በኋላ፥
2፤ ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎች ከእስራኤል መረጠ፤ ሁለቱም ሺህ በማክማስና በቤቴል ተራራ ከሳኦል ጋር ነበሩ፥ አንዱም ሺህ በብንያም ጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ፤ የቀረውንም ሕዝብ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ አሰናበተ።
3፤ ዮናታንም በናሲብ ውስጥ የነበረውን የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መታ፥ ፍልስጥኤማውያንም ያን ሰሙ፤ ሳኦልም። ዕብራውያን ይስሙ ብሎ በአገሩ ሁሉ ቀንደ መለከት ነፋ።
4፤ እስራኤልም ሁሉ ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ እንደ መታ፥ ደግሞም እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ተጸየፉ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ።
5፤ ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ተሰበሰቡ፤ ሠላሳ ሺህ ሰረገሎች ስድስትም ሺህ ፈረሰኞች በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበሩ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በምሥራቅ በኩል በማክማስ ሰፈሩ።
6፤ ሕዝቡም ተጨንቀው ነበርና የእስራኤል ሰዎች በጭንቀት እንዳሉ ባዩ ጊዜ ሕዝቡ በዋሻና በእሾህ ቍጥቋጦ በገደልና በግንብ በጕድጓድም ውስጥ ተሸሸጉ።
7፤ ከዕብራውያንም ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ፤ ሳኦል ግን ገና በጌልገላ ነበረ፥ ሕዝቡም ሁሉ ተንቀጥቅጠው ተከተሉት።
8፤ ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ጊዜ ሰባት ቀን ቆየ፤ ሳሙኤል ግን ወደ ጌልገላ አልመጣም፥ ሕዝቡም ከእርሱ ተለይተው ተበታተኑ።
9፤ ሳኦልም። የሚቃጠል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት አምጡልኝ አለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ።
10፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በፈጸመ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲመርቀው ሊገናኘው ወጣ።
11፤ ሳሙኤልም። ያደረግኸው ምንድር ነው? አለ። ሳኦልም። ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፥ አንተም በቀጠሮው እንዳልመጣህ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ማክማስ እንደ ተሰበሰቡ አየሁ፤
12፤ ሰለዚህ። ፍልስጥኤማውያን አሁን ወደ ጌልገላ ይወርዱብኛል፥ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም አልሁ፤ ስለዚህም ሳልታገሥ የሚቃጠልን መሥዋዕት አሳረግሁ አለ።
13፤ ሳሙኤልም ሳኦልን። አላበጀህም፤ አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጽንቶልህ ነበረ።
14፤ አሁንም መንግሥትህ አይጸናም፤ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል፤ እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዞታል አለው።
15፤ ሳሙኤልም ከጌልገላ ተነሥቶ መንገዱን ሄደ፤ የቀሩትም ሕዝብ ሳኦልን ተከተለው ሰልፈኞቹን ሊገናኙ ሄዱ። ከጌልገላም ተነሥተው ወደ ብንያም ጊብዓ መጡ፤ ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ስድስት መቶም የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ።
16፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ከእነርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ በብንያም ጊብዓ ተቀመጡ፤ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ ሰፈሩ።
17፤ ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር ማራኪዎች በሦስት ክፍል ሆነው ወጡ፤ አንዱም ክፍል በዖፍራ መንገድ ወደ ሦጋል ምድር ሄደ።
18፤ ሁለተኛው ክፍል ወደ ቤት ሖሮን መንገድ ዞረ፤ ሦስተኛውም ክፍል በበረሃው አጠገብ ባለው ወደ ስቦይም ሸለቆ በሚመለከተው በዳርቻ መንገድ ዞረ።
19፤ ፍልስጥኤማውያንም። ዕብራውያን ሰይፍና ጦር እንዳይሠሩ ብለው ነበርና በእስራኤል ምድር ሁሉ ብረተ ሠሪ አልተገኘም።
20፤ እስራኤልም ሁሉ የማረሻውን ጫፍና ማጭዱን መጥረቢያውንና መቆፈሪያውን ይስል ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርድ ነበር።
21፤ ለማረሻው ጫፍና ለመቆፈሪያው ዋጋው የሰቅል ከ3 እጅ 2ቱ እጅ ነበረ። መጥረቢያውንም ለማሳል መውጊያውንም ለማበጀት ዋጋው የሰቅል ከ3 እጅ 1ዱ እጅ ነበረ።
22፤ ስለዚህም በሰልፍ ቀን ሰይፍና ጦር ከሳኦልና ከዮናታን ጋር በነበሩ ሕዝብ ሁሉ እጅ አልተገኘም፤ ብቻ በሳኦልና በልጁ በዮናታን ዘንድ ተገኘ። የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ ወደ ማክማስ መተላለፊያ ወጡ።
23