ምዕራፍ 2
1፤ ለኑኃሚንም ባል የሚዘመደው ከአቤሜሌክ ወገን የሆነ ኃያል ሰው ስሙ ቦዔዝ የተባለ ሰው ነበረ።
2፤ ሞዓባዊቱም ሩት ኑኃሚንን። በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ አለቻት። እርስዋም። ልጄ ሆይ፥ ሂጂ አለቻት።
3፤ ሄደችም፥ ከአጫጆችም በኋኋኋ ላ በእርሻ ውስጥ ቃረ እንደ አጋጣሚውም የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች።
4፤ እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፥ አጫጆችንም። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር ይባርክህ ብለው መለሱለት።
5፤ ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን ሎሌውን። ይህች ቆንጆ የማን ናት? አለው።
6፤ የአጫጆቹም አዛዥ። ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ቆንጆ ናት፤
7፤ እርስዋም። ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ አለች፤ መጣችም፥ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ድረስ ቆይታለች፤ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም አለው።
8፤ ቦዔዝም ሩትን። ልጄ ሆይ፥ ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፥ ከዚህም አትላወሺ፥ ነገር ግን ገረዶቼን ተጠጊ።
9፤ ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፥ ተከተያቸውም፤ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፤ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውኃ ጠጪ አላት።
10፤ በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት። እኔንስ ለመቀበል በምን ነገር በፊትህ ሞገስ አገኘሁ? እኔ እንግዳ አይደለሁምን? አለችው።
11፤ ቦዔዝም። ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ።
12፤ እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፤ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ደመወዝሽ ፍጹም ይሁን አላት።
13፤ እርስዋም። ጌታዬ ሆይ፥ ከባሪያዎችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኸኛልና፥ የባሪያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዓይንህ ሞገስ ላግኝ አለችው።
14፤ በምሳም ጊዜ ቦዔዝ። ወደዚህ ቅረቢ፤ ምሳ ብዪ፥ እንጀራሽንም በሆምጣጤው አጥቅሽ አላት። በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች የተጠበሰም እሸት ሰጣት፥ በልታም ጠገበች፥ አተረፈችም።
15፤ ደግሞም ልትቃርም በተነሣች ጊዜ ቦዔዝ ጐበዛዝቱን። በነዶው መካከል ትቃርም፥ እናንተም አታሳፍሩአት፤
16፤ ደግሞ ከነዶው አስቀርታችሁ ተዉላት፤ እርስዋም ትቃርም፥ አትውቀሱአትም ብሎ አዘዛቸው።
17፤ በእርሻውም ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፤ የቃረመችውንም ወቃችው፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ያህልም ገብስ ሆነ።
18፤ ተሸክማውም ወደ ከተማ ገባች፥ አማትዋም የቃረመችውን አየች፤ ከጠገበችም በኋላ የተረፋትን አውጥታ ሰጠቻት።
19፤ አማትዋም። ዛሬ ወዴት ቃረምሽ? ወዴትስ ሠራሽ? የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን አለቻት። እርስዋም። ዛሬ የሠራሁበት ሰው ስም ቦዔዝ ይባላል ብላ በማን ዘንድ እንደ ሠራች ለአማትዋ ነገረቻት።
20፤ ኑኃሚንም ምራትዋን። ቸርነቱን በሕያዋንና በሙታን ላይ አልተወምና በእግዚአብሔር የተባረከ ይሁን አለቻት። ኑኃሚንም ደግሞ። ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው፥ እርሱም ሊቤዡን ከሚችሉት አንዱ ነው አለቻት።
21፤ ሞዓባዊቱ ሩትም። ደግሞ። መከሬን እስኪጨርሱ ድረስ ጐበዛዝቴን ተጠጊ አለኝ አለቻት።
22፤ ኑኃሚንም ምራትዋን ሩትን። ልጄ ሆይ፥ ከገረዶቹ ጋር ብትወጪ፥ በሌላም እርሻ ባያገኙሽ መልካም ነው አለቻት።
23፤ ሩትም የገብሱና የስንዴው መከር እስኪጨረስ ድረስ ልትቃርም የቦዔዝን ገረዶች ተጠጋች፤ በአማትዋም ዘንድ ትቀመጥ ነበር።