ምዕራፍ 1
1፤ እግዚአብሔርም ከመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሙሴን ጠርቶ እንዲህ ሲል ተናገረው።
2፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራችው። ከእናንተ ማናቸውም ሰው ለእግዚአብሔር መባ ሲያቀርብ መባችሁን ከእንስሳ ወገን ከላሞች ወይም ከበጎች ታቀርባላችሁ።
3፤ መባውም የሚቃጠል መሥዋዕት ከላሞች መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርባል፤ በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ያቀርበዋል።
4፤ እጁንም በሚቃጠለው መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ ያስተሰርይለትም ዘንድ የሠመረ ይሆንለታል።
5፤ በሬውንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን ያቀርባሉ፤ ደሙንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ባለው በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል።
6፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ይገፍፈዋል፥ በየብልቱም ይቈርጠዋል።
7፤ የካህኑም የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ እሳት ያነድዳሉ፥ በእሳቱም ላይ እንጨት ይደረድራሉ፤
8፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የተቈረቱትን ብልቶች ራሱንም ስቡንም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርቡታል፤
9፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል፤ ካህኑም ሁሉን የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን አድርጎ በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።
10፤ ቍርባኑም የሚቃጠል መሥዋዕት ከበጎች ወይም ከፍየሎች ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርበዋል።
11፤ በመሠዊያውም አጠገብ በሰሜን ወገን በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል።
12፤ በየብልቱም ራሱንም ስቡንም ይቈርጠዋል፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርበዋል፤
13፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል። ካህኑም ሁሉን አቅርቦ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ ነው።
14፤ ለእግዚአብሔርም የሚቀርበው ቍርባን የሚቃጠል መሥዋዕት ከወፎች ቢሆን፥ ቍርባኑን ከዋኖስ ወይም ከርግብ ያቀርባል።
15፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል፥ ራሱንም ይቈለምመዋል፥ በመሠዊያውም ላይ ያቃጥለዋል። ደሙም በመሠዊያው አጠገብ ይንጠፈጠፋል፤
16፤ የሆድ ዕቃውንም ከላባዎች ጋር ለይቶ በመሠዊያው አጠገብ በምሥራቅ ወገን በአመዱ ስፍራ ይጥለዋል፤
17፤ በክንፎቹም ይቀድደዋል፥ ነገር ግን አይከፍለውም። ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥለዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ ነው።